ስሜ  ሙላቱ  ላንቴ  ይባላል ፡፡ እድሜዬን  ለማስታወስ ይቸግረኛል፡፡ የተወለድኩት  መራ ቤቴ  አውራጃ  ነው፡፡ እናቴ  እኔን እንደወለደች  ነው  የሞተችው፡፡ እኔን፤ እህቶቼንና  ወንድሞቼን ያሳደገን  አባታችን  ሲሆን የገጠር   ህይወት  በመሆኑ  በልጅነት  መዳር  የተለመደ  ነበር፡፡አገር ቤት እያለሁ ሶስት ልጆች ወልጄ ነበር፡፡ ሁለቱን በማደግ ላይ እያሉ ሞት ነጠቀኝ፤ባለቤቴንም እንዲሁ፡፡ አንዱ የቀረኝን ልጄን ወንድሜ ማሳደግ ጀመረ፡፡ ዘመዶቼ በሙሉ በማለቃቸው ሀዘን ውስጥ እንዳለሁ፤ አዲስ አበባ የምትኖረው የአጎቴ ልጅ ካልወሰድኩሽ ብላ ለምና አመጣችኝ፡፡ በመጀመሪያ የማያውቁት አገር አይናፍቅም በማለት አሻፈረኝ ብልም ያለሁበትን ሁኔታ በማሰብ እሱዋን ተከትዬ መጣሁ፡፡

አዲስ አበባ የገባሁት በጃንሆይ ዘመነ መንግስት ነበር፡፡ እዚህም ሁለተኛ ባል አግብቼ ልጆች ወልድኩ፡፡ ኑሮአችንን እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ እንኖር ነበር፡፡ ነገር ግን ከሁለተኛው ባሌ የወለድኳቸው ሁለት ልጆቼ በደርግ ዘመነ መንግስት በብሄራዊ ውትድርና ተወስደው ሳይመለሱ ቀሩ፡፡ በሀዘን ለብዙ ጊዜያቶች ተሰቃይችለሁ፡፡ ሁለተኛው ሶስት  ልጆችን ወልዶ ነበር፡፡ ባለቤቴንም እንዲሁ በሞት ተነጠኩ፡፡ከዚያ ጊዜ በሁዋላ ልጄን እየተመላለስኩ እጠይቀው ነበር፡፡ እንዲሁም እየመጡ የሚጠይቁኝ ዘመዶች ነበሩኝ፡፡ በዚያን ጊዜ የራሴን ሆድ ለመሙላት አልቸገረኝም ነበር፡፡ከጊዜ በሁዋላ ግን አይኖቼ እይታቸው እየደበዘዘ በመምጣቱ እንረዳዳ አረጋውያን ማህበር ህክምና ድጋ አድርጎልኝ የታከምኩ ሲሆን  ነገር ግን የአይኖቼን እይታ መልሼ ላገኝ አልቻልኩም፡፡ ያልሄድኩበት ሃኪም ቤት ያልሄድኩበት ጸበል አልነበረም፡፡ የአምላክ ፈቃድ ባለመሆኑ ሳይሳካ ቀረ፡፡እናም አይኖቼ ጤነኛ እያሉ እሰራ የነበሩትን ስራዎች መስራት አቃተኝ፡፡ ታክሲ እያለ በእግር እሄድ የነበርኩት ከቤት እንኩዋን መውጣት የማይቻል ሆነብኝ፡፡ በዛ ትልቅ ችግር ውስጥ እያለሁ ጎረቤቶቼ ካጠገቤ ሳይለዩ ይረዱኝ ነበር፡፡ አሁን የምኖርበትንም ቤት እነደዚሁ በነጻ ነው የሰጡኝ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ነበር አንድ የጎረቤት ልጅ እንረዳዳ የአረጋውያን መርጃ ድርጅት ያስመዘገበኝ፡፡ ምግቤን የማበስለው ከዚሁ ድርጅት በየወሩ በሚደረግልኝ ድጋፍ  ነው፡፡ የምኖረው በሰዎች እርዳታ ነው፡፡ እንጀራ የሚጋግሩልኝ የጎረቤት ልጆች ናቸው፡፡ እኔም ለመስራት የማይከብዱ ምግቦችን እሰራለሁ፡፡ በአጠቃላይ በእግዚአብሔር ረዳትነት እኖራለሁ፡፡